251CHECK
This article was fact-checked by a professional who adheres strictly to established fact-checking principles and processes.
“ሀሰት፡ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ወደ አሜሪካ ኮበለሉ የሚለው መረጃ የተሳሳተ ነው”
ሀቅሰሚ ከሰሞኑ ከሀገራዊ ምክክሩ ጋር በተያያዘ በነሀሴ ቀን 2018 ዓ.ም Zene Manchester በተሰኘ እና ከ7000 በላይ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ገፅ እንዲሁም በ Ethio Politics Unity እና Anchor Media በተሰኙ ገጾች “የምክክር ኮሚሽን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከመጨረሻው የውሳኔ ቀን በፊት ወደ አሜሪካ ፈርጥጠው ገብተዋል” በማለት የተሰራጩ መረጃዎችን ተመልክቷል። ይህ መረጃ ከተሰራጨ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ መጋራትና እይታ ያገኘ ሲሆን፣ ከ3000 በላይ ላይክ ፣ 600 በላይ አስታያየቶችን እና ከ160 በላይ መጋራትን በማግኘት በማህበራዊ ሚዲያው ማህበረሰብ ዘንድ ብዥታ ሲፈጥር አስተውለናል።
በተጨማሪም፣ “Ethiopian DJ የኢትዮጵያ ሙዚቃ” በተሰኘ ሌላ ገጽ ደግሞ ምስሉን በመጠቀም “የአንድነት ዜና!” በሚል ርዕስ “አፋብኃ እና አፋሕድ አንድነት ለመፍጠር መስማማታቸውን ምንጮች ገለፁ” የሚል መግለጫ አውጥቷል። ይህ ፖስት ከ2,100 በላይ ሪአክሽኖችን እና 38 መጋራቶችን በማግኘት በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሮ ነበር፤ ይህም አብዛኛው አስተያየት ሰጪዎች ምስሉ እውነት መሆኑን አምነው “በርቱልን” የሚል መልዕክት እንዲያጋሩ አድርጓል።
ምስል 2፤ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከውሳኔ በፊት ኮብልለዋል በመባል የተሰራጨ መረጃ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ ባሉ መሠረታዊ እና አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ በህዝብና በፖለቲካ ሀይሎች መካከል ሰፊ ውይይት በማድረግ ዘላቂ መግባባት ለመፍጠር በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም ነው።
የኮሚሽኑ ዋና ዓላማም እንደ ህገ-መንግስት፣ የፌደራሊዝም ቅርፅ፣ የታሪክ ትረካዎች እና የወሰን ጥያቄዎች ባሉ አከራካሪ ርዕሶች ላይ በስፋት በመወያየት የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ሲሆን ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ልዩነቶችን በኃይል ፈንታ በሰለጠነ የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር የማስወገድ ባህልን ማዳበር ነው::
ይህንን ዓላማ ለማሳካት ኮሚሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማህበራትን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ አሳታፊ የምክክር መድረኮችን ያዘጋጃል። በዚህ ሂደት የተለዩ አጀንዳዎችን እና የተሰበሰቡ የውሳኔ ሀሳቦችን አጠቃሎ ለህዝብና ለሚመለከታቸው አካላት የሚያቀርብ ይሆናል።
ተቋሙን በዋና ኮሚሽነርነት የሚመሩት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የረጅም አመታት የምርምር ልምድ ያላቸው ታዋቂ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን በኃላፊነት ሲመሩ ቆይተዋል።
ምሳል 2፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋናው አገራዊ የምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መረሀ ግብር የተወሰደ
ሀቅሰሚ ባደረገው የማጣራት ስራ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የምክክር ኮሚሽኑን ጥለው ኮበለሉ የሚለው መረጃ መሰረት የሌለው መሆኑን አረጋግጧል።
ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ፣ ፕሮፌሰሩ ወደ አሜሪካ አቅንተው የነበረው በቤተሰብ ድንገተኛ ሁኔታ (የእህታቸው ህልፈት) ምክንያት እንጂ ሀገር ጥለው ለመኮብለል እንዳልሆነ ከምክክር ኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል።
በሁለተኛ ደረጃ፣ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በጉባኤው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ በአካል በመገኘት ሂደቱን እየመሩ ይገኛሉ። ፕሮፌሰሩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ሀሰተኛ መረጃውን ያስተባበሉ ሲሆን፤ “የነበርኩበትን ሁኔታ ተረድታችሁኛል፣ ከሀገር አልሸሸሁም፤ ከሀገሬ መቸም አልሸሸሁም። ከሀገሬም አልኮበለልኩም። እንኳን በዚህ ዕድሜዬ የዛሬ 40 ዓመት ጉልበት በነበረኝ ጊዜ መውጣት በሚቻልበት ጊዜ ወንድሞቼ ውጭ በነበሩበት እና ‘ና’ ባሉኝ ጊዜም ከሀገሬ አልወጣሁም። እና የቀረችኝን ዕድሜ እዚሁ ነው የማሳልፈው” በማለት ሀገር ጥለው እንዳልኮበለሉ በራሳቸው አንደበት አረጋግጠዋል።
ምሳል 3፤ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በሀገራዊ የምምክር መደረክ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ የተወሰደ ምስል
በሦስተኛ ደረጃ፣ የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ነሐሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት ይፋዊ መግለጫ፣ ኮሚሽኑ ከ120 በላይ አጠናቃሪ ተሳታፊዎችን በማስተባበር የውይይት ሰነዶችን አጠናቆ ለ4 ሺህ ተሳታፊዎች ለማቅረብ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝና ሂደቱ በተያዘለት ሰሌዳ መሰረት እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ በበይነ መረብ ላይ ያገኘናቸው መረጃዎች ፕሮፌሰሩ የእህታቸውን ሰብለ ጌታቸውን የቀብር ስነ-ስርዓት ነሀሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ለመታደም በአሜሪካ ሜሪላንድ እንደነበሩ የሚያሳዩ መረጃዎችን ማግኘት ተችሏል። በጥሪ መግለጫው ላይም የፕሮፌሰሩ ስም በጽሁፉ ግርጌ ስር ሰፍሮ እናገኘዋለን።
ምሳል 4፤ በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት የሚፈጸመውን የኮሚሽነሩን እሀት የቀብር ስነ-ስርዓት ጊዜ እና ቦታ የሚያሳይ
ማጠቃለያ፦
ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ሀገር ጥለው ኮበለሉ በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መረጃ የተፈበረከ እና ሀሰተኛ መሆኑን ሀቅሰሚ ማረጋገጥ ችሏል።
What do you feel? የተሰማችሁን አጋሩን
We hope you found this article insightful. Our goal is to provide clear and accurate information, but we know there’s always room for improvement. If you have feedback or suggestions for us, we’re all ears!
Let’s Work Together ! የተዛባ መረጃን በጋራ እንከላከል!
Together, we can combat misinformation. Let’s join forces and make sure everyone has access to reliable information.