251CHECK
This article was fact-checked by a professional who adheres strictly to established fact-checking principles and processes.
“ዘመነ ካሴና እስክንድር ነጋ ተወያዩ” የተባለው ምስል በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የተፈበረከ ነው”
በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲዘዋወር የነበረው፣ የፋኖ አመራሮች የሆኑት ዘመነ ካሴ እና እስክንድር ነጋ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እየመከሩ የሚያሳይ ምስል ሙሉ በሙሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የተፈጠረ መሆኑን የኛ የማጣራት ቡድን አረጋግጧል። ይህ ሐሰተኛ መረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳስቶ ከፍተኛ መስተጋብርን (engagement) አግኝቶ ነበር።
የሐሰት ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው በህዳር 15 ላይ ከ248 ሺሕ በላይ የፌስቡክ ተከታይ ባለው የፖለቲካ ሰው ደረጀ ሃብተወልድ የፌስቡክ ገጽ ሲሆን፣ “እንዲህ ነው የሚያምርብን፤ ይህ ፎቶ በራሱ ለአራት ኪሎዎች ‘ሄሞራጅክ ፊቨር’ ነው” በሚል ገላጭ ጽሑፍ ታጅቦ ነበር። ይህ ፖስት ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ከ3,800 በላይ ሪአክሽኖችን፣ ከ17 በላይ አስተያየቶችን እና ከ119 በላይ መጋራቶችን አግኝቷል።
በተጨማሪም፣ “Ethiopian DJ የኢትዮጵያ ሙዚቃ” በተሰኘ ሌላ ገጽ ደግሞ ምስሉን በመጠቀም “የአንድነት ዜና!” በሚል ርዕስ “አፋብኃ እና አፋሕድ አንድነት ለመፍጠር መስማማታቸውን ምንጮች ገለፁ” የሚል መግለጫ አውጥቷል። ይህ ፖስት ከ2,100 በላይ ሪአክሽኖችን እና 38 መጋራቶችን በማግኘት በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሮ ነበር፤ ይህም አብዛኛው አስተያየት ሰጪዎች ምስሉ እውነት መሆኑን አምነው “በርቱልን” የሚል መልዕክትእንዲያጋሩ አድርጓል።
ምስሉ የተለያየ አመለካከትና ትግል ሲያካሂዱ በነበሩት የፋኖ አመራሮች መካከል ስምምነት መኖሩን የሚያሳይ በመምሰል፣ በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሱት የፋኖ ኃይሎች ውስጥ የነበረውን ልዩነት አስቀርቷል የሚል አዎንታዊ ግምት እንዲፈጠር አድርጓል።
ይህንን ምስል በተመለከተ እውነታውን ለማጣራት የጎግል ተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ (Google Reverse Image Search) እና TinEye የተሰኙ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። በእነዚህ ፍለጋዎች ምስሉ ከዚህ ቀደም በሌላ ቦታ ጥቅም ላይ የዋለበት አውድ አለመገኘቱ፣ አዲስ የተፈጠረ ሆኖ አግኝተነዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ምስሉን በAI Image Detector መሳሪያ ላይ በማስቀመጥ በተደረገው ማጣራት፣ ምስሉ ሙሉ በሙሉ በሰው ሰራሽ ክሕሎት እንደተፈበረከ የማያሻማ ማረጋገጫ ተገኝቷል።
የዘመነ ካሴንና የእስክንድር ነጋን የፊት ገጽታ ወደ AI ምስል ፈጣሪ በማስገባት እንዲሁም እስክርቢቶ፤ ወረቀት እንዲሁም የሻይ ካፕ በመጨመር እነሱን እንዲመሳሰሉ በማድረግ የተፈጠረ ምስል መሆኑ ተመላክቷል።
ይህ የሚያሳየው፣ በቅርብ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው AI ቴክኖሎጂ፣ እውነተኛ የሚመስሉ ነገር ግን ፈጽሞ ያልተከሰቱ ሁኔታዎችን የሚወክሉ ምስሎችን በመፍጠር ሐሰተኛ መረጃ (disinformation) የማሰራጨት አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ነው።
ሚዲያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ማንኛውንም ከፍተኛ ስሜት ቀስቃሽ መረጃ ከማጋራታቸው በፊት ጥልቅ ማጣራት ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ይህ ክስተት ያሳስባል።
What do you feel? የተሰማችሁን አጋሩን
We hope you found this article insightful. Our goal is to provide clear and accurate information, but we know there’s always room for improvement. If you have feedback or suggestions for us, we’re all ears!
Let’s Work Together ! የተዛባ መረጃን በጋራ እንከላከል!
Together, we can combat misinformation. Let’s join forces and make sure everyone has access to reliable information.